የእምነት መግለጫ

መጽሐፍ ቅዱስ ባጠቃላይ 66 መጻሕፍትን የያዘ፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በቅዱሳን ሰዎች በእስትንፋሰ መለኮት ተጽፎ የተጠናቀቀ፣ የማይለወጥ፣ ስህተት አልባ፣ የእግዚአብሄር ቃል እንደሆነ እናምናለን። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሥልጣን ያለዉ፣ ለድነት፣ ለህይወት፣ ለእምነትና ለበጎነት/ቸርነት ሁሉ የበላይ መመሪያችን ሲሆን፣ በቀጥተኛ፣ በሰዋሰዋዊና በታሪካዊ አተረጏገሙ ብቁ የሆነ ማማከሪያችን ነዉ።

በሦስት አካል በተገለጠ፤ሁሉን በፈጠረ፤ ሰዎችን ከጥፋት በሚያድን፤ በአብ፤ በወልድ፤ በመንፈስ ቅዱስ አንድ ዓምላክ እናምናለን፤አብ ወልድ አይደለም፣ አብ መንፈስ ቅዱስ አይደለም፤ ወልድ አብ አይደለም፤ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስ አብ አይደለም፣ መንፈስ ቅዱስ ወልድ አይደለም፤ አሃዱ አምላክ ከመረዳት በላይ በሆነ መለኮታዊና መንፈሳዊ አንድነት የሚኖር እንደሆነ እናምናልን።

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሄር አንዲያ ልጅ፣ ሁሉ በርሱ ለርሱ የተፈጠረ፣ ብቸኛ የሃጢአት ማስተሰሪያ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰዉ ሆኖ የተገለጠ፣ በመንፈስ ቅዱስ በተጸነሰ፤ ከድንግል ማርያም በተወለደ፤ኅጢሃት በሌለዉ፤ በሞተ፤ በተቀበረ፤ በሦስተኛዉ ቀን ከሙታን በተነሣ፣ ባረገና በአብ ቀኝ በተቀመጠ፣ የቤተ ከርስቲያን ራስ በሆነ፣ በዘመን መጨረሻ እንደ ጌታና እንደንጉስ በአካል በሚመለስ፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን።

ቅዱስ አምላክ እንደሆነ ሰዉን ስለሃጢአት በሚወቅስና ለአዲስ ልደት በሚያበቃ፣ በአማኞች በሚኖር፣ በሚያትመን፣ በሚመራን፣ ለመልካም ህይወትና ለአገልግሎት ሃይል በሚሰጠን፣ እናምናለን። መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ መጻሕፍትን በሰዎች የጻፈ፣ የእግዚአብሄርን ቃል ለእምነትና ለመረዳት የሚገልጥ፣ አማኞችን በድነት ጊዜ የሚያጠምቅ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ አማኞችን የሚሞላ እንደሆነ እናምናለን።

ሰው በእግዚአብሄር አምሳያ እንደተፈጠረ፣ በሃጢአት ምክንያት ቅንነቱን እንዳጣና ሞትን እንደሞተ፣ ራሱን ማዳን የማይችል፣ ሁሉ ሃጢአተኛ እንደሆነ፣ በከርስቶስ ጸጋ ብቻ በክርስቶስ ህይወት፣ ሞትና ትንሳኤ በእምነት ብቻ እንድሚድን እናምናለን።

የሰዉ ልጅ ድነት በእግዚአብሄር መለኮታዊ ምርጫና በዳግም ልደት ንሥሃ በመግባትና በማመን እንደሆነ እናምናለን።

በእዉነት የዳነ ሰዉ ሁሉ ከሃጢአት መራቅና መቀደስ እንዳለበት እናምናለን። ወዲያዉም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ ክርስቶስ አካል (ቤተ-ከርስቲያን) እንደሚጨመር እናምናለን።

በዉስጥ የመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት በዉጪ የጽድቅና እዉነተኛ የቅድስና ህይወቱ የአንድ አማኝ የመዳን መረጃዎች እንደሆኑ እናምናለን። የክርስትና ዋስትናም ከእግዚአብሄር ምርጫ እንደሚመነጭ እናምናለን።

በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እናምናለን።

በመለኮታዊ ፈዉስ እናምናለን። ይህም፤ በክርስቶስ በማመናችን የሚገኘዉ ጥቅም አካል ነዉ

መንፈስ ቅዱስ ቅዱሳንን ለማነጽና ፍጹማን ለማድረግ እንደወደደ ስጦታዎችን ከመጀመሪያ ቤተ-ክርስቲያን ጀምሮ እስከ ዛሬ የሚሰጣቸዉ እንዳሉም እናምናለን። የሃዋሪያነትን ሥራ ለማጽናት ብቻ የተሰጡ ተአምራዊ ስጦታዎችም እንዳሉና በዛሬ ዘመን ለቤተ-ክርስቲያን የማይሰጡ ስጦታዎች እንዳሉም እናምናለን።

በሙታን ትንሳኤ እናምናለን፤ ይህም ጌታ ዳግም ሲመጣ የሚሆን የተቀደሰ ተስፋችን ነዉ የዳኑት ለዘለላም ሕይወት፤ ያልዳኑት ለዘላለም ሞት ፍርድ፣ የሙታን ትንሣኤ ይሆናል። ብለን እናምናለን።

ዳግም ምጻት ከቅዱሳን መነጠቅ ጋር አብሮ የሚከሰት መሆኑን እናምናለን። ይህም፤ የተቀደሰ ተስፋችን ሲሆን ቀጥሎም ጌታችን ለመንግሥቱ ሺ ዓመት ግዛት በግልጽ ይመጣል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ስለሽማግሌዎች የተጻፈዉን እንዲሁም ቤተ-ክርስቲያንን ከክርስቶስ በታች ይመሩና ያስተዳድሩ ዘንድ የተመደቡት ሽማግሌዎች እንደሆኑ እናምናለን። እነዚህ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ስሞች ተጠርተዉ እናገኛለን (Bishops, Overseers, Pastors…)። የክርስቶስን መንጋ እንዲጠብቁና በምሳሌነት እንዲመሩ ሽማግሌዎችን ለቤተ ከርስቲያን የሚሾመዉ እግዚአብሄር እንደሆነ እናምናለን። እነዚህ ሽማግሌዎች እንደ መንጋ ጠባቂ ወይም እረኛ ወይም መሪ ያገለግላሉ። እግዚአብሄር የሚሾማቸዉን አገልጋዮች መንጋዉ እንዲያዉቅላቸዉ እንዲተባበሯቸዉ ታዟል። መልካሙ እረኛ ጌታ ኢየሱስ ሲሆን ከእርሱ በታች መንጋዉን የሚጠብቁ እረኞች የአጥቢያ ቤተ-ክርስቲያን ሽማግሌዎች ናቸዉ።

ዲያቆናትም የመጽሐፍ ቅዱስን መስፈርቶች የሚያሟሉ ሆኖ ከሽማግሌዎች በታች ቤተ-ክርስቲያንን ለሥጋዊና አስተዳደራዊ ፍላጎቶች ያገለግላሉ።

ሴይጣን በእግዚአብሄር የተፈጠረ መልአክ ሃጢአትንና አመጻን አድርጎ ከሌሎች መላእክት (አጋንንት) ጋር ከክብሩ የወደቀ እንደሆነ እናምናለ፣ ከዚያም በኤደን ገነት ሔዋንን በመፈተን ወደ ሃጢአት ያጋባ የሰዉን ልጅ ያሳተ ፍጡር እንደሆነ እናምናለን። ሴይጣን የእግዚአብሄርና የሰዉ ጠላት የዚህ ምድር ገዢ እንደሆነ በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ የተሸነፈ እንደሆነ፣ በመጨረሻም በገሃነም እሳት ዘላለማዊ ፍርድ እንድሚጠብቀዉ እናምናለን።

አእላፍ መላዕክት እንዳሉና በማይጠፋ ክብር በሰማይ የሚኖሩና ሳያቇርጡ እግዚአብሄርን እንድሚያመልኩ፣ በእግዚአብሄር ትዕዛዝ ክርስቲያኖችን እንድሚያገለግሉ እናምናለን። እነዚህም ቅዱሳንና የተመረጡ መላዕክት የእግዚአብሄር የፀጋዉ ሥራ ክብርና ጥበብ የሚገለጥባቸዉ እንደሆኑ አማኞችንና ትናንሾችን እንደሚጠብቁ፣ ቤተ ክርስቲያንም ዉስጥ የሚሆነዉን የሚከታተሉ እንደሆኑ እናምናለን። መላእክት በአባቶች ዘመን፣ በህግ መሰጠት፣ በክርስቶስ ልደት፣ ትንሳኤ እና እርገት እንዳገለገሉ፣ በዳግም ምጻቱም እንደሚያገለግሉ እናምናለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish